የስልጤ ህዝብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ መንግስት ከሚገኙ ብሄረሰቦች መካከል አንዱ ሲሆን ድንቅ ባህል፣ አኗኗርና ልዩ ልዩ ታሪኮች ያሉት ማህበረሰብ ነዉ፡፡ ለአብነት የብሄረሰብ ማንነቱን ለማግኘት ያደረገዉን የትግል ዳራ ማንሳቱ በቂ ማሳያ ነው፡፡ የዞኑ አጠቃላይ የመሬት ስፋት 2700.04 ስ/ኪ/ሜ ሲሆን የህዝብ ቁጥር በ2015 መጨረሻ ከ1.28 ሚሊየን በላይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ ለዘመናት ማንነቱ ተነፍጎ በ3 የአስተዳደራዊ ቀጠና ተከፋፍሎ ሲገዛ እንደነበር የቅርብ ጊዜ የታሪክ ትዉስታ ነዉ፡፡
ይህን ታሪክ በመሰረቱ በመቀየር ረገድ በተደረገዉ የትግል ሂደት በርካታ የማንነት ታጋዮችና አጠቃላይ ማህበረሰቡም ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ህይወቱን ጭምር መስዋዕትነት የከፈለ ሲሆን የኃላም ጀግኖች የተሰዉለት የማንነት ጥያቄ ህገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ መጋቢት 23/1993 በተደረገው ህዝበ ዉሳኔ ፍሬ በማፍራቱ ዛሬ ላይ እየገነባነዉ ላለዉ ዞናዊ እድገት መሰረት ሆኗል፡፡ አሁን ላይ ዞኑ በአዲስ መልኩ ከተደራጀ በኋላ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ስር ከተዋቀሩት 7 ዞኖችና 3 ልዩ ወረዳዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
የስልጤ ዞን በደቡብ ምስራቅ የሀላባ ዞን፤ በሰሜን ምስራቅ ጉራጌ ዞን፣ በምዕራብ ጉራጌ ዞን፣ በምስራቅ ኦሮሚያ ክልል፣ በደቡብ ሀድያ ዞንና በሰሜን ምስራቅ ማረቆ ልዩ ወረዳ ያዋስኑታል፡፡ የዞኑ ዋና ከተማ ወራቤ ከተማ ስትሆን ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በ172 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች:: ዞኑ አስትሮኖሚካል መገኛው 700431-800101 ሰሜን ላቲቲውድ እና 370861 -380531 ምስራቅ ሎንግቲውድ ላይ ይገኛል፡፡
የስልጤ ዞን አጠቃላይ 2700.04 ስኩዌር ኪ.ሜ ስፋት ያለው ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለእርሻ ያዋለው 198587.05 (165027.27 በዓመታዊ ሰብልና 33557.5 በቋሚ ሰብል የተሸፈነ)፤ ሊለማ የሚችለው 8319፤ ሊለማ የማይችለው 4759.17፤ ለግጦሽ አግልግሎት የዋለ 10646.67፤ ደንና ቁጥቋጦ 29187.47 ውሃና ረግረጋማ ሥፍራ 8832.84 ና የቀረው 12423.72፤ በሌሎች ልዩ ልዩ ይዞታዎች የተሸፈነ ነው፡፡ አስተዳደራዊ አወቃቀርም በ10 ወረዳዎችና በ5 ከተማ አስተዳደሮች ሲሆን (ዳሎቻ፤ ሁልባራግ፤ ስልጢ፤ ምስራቅ ስልጢ፤ ላንፉሮ፤ ሚቶ፤ አሊቾ-ውሪሮ፤ ሳንኩራ፤ ምዕራብ አዘርነት በርበሬ፤ ምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳዎችና ወራቤ፤ ቅበት፤ ጦራ፤ ዓለምገበያ እና ዳሎቻ ከተማ አስተዳደር) የሚገኙ ሲሆን እንዲሁም ዞኑ በ36 የከተማ ቀበሌያትና በ200 የገጠር ቀበሌያት የተደራጀ ነው፡፡
የስልጤ ዞን መልካዓ-ምድራዊ ገጽታ በአመዛኙ ሜዳማ ሲሆን ቀሪው ክፍል በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደን የተሸፈነ ተራራማና ገደላገደላ ገጽ አለው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ምዕራባዊ ክንፍ ምዕራብና ምስራቅ አዘርነት በርበሬንና አሊቾ ውሪሮ ወረዳን ወደ ምዕራብ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ የሚገኙትን ስልጢ፤ ዳሎቻ፤ ሁልባራግ፤ ላንፉሮ፤ ምስራቅ ስልጢ፤ ሚቶና ሳንኩራ ወረዳዎችንና ወራቤ፤ ቅበት፤ ጦራ፤ ዳሎቻና ዓለም ገበያ ከተማ አስታዳደርን ወደ ምስራቅ በመተው ለሁለት ይከፍለዋል፡፡
አጠቃላይ የዞኑ ከፍታ ከ1500-3700 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ሲሆን በክልሉ ካሉ ከፍተኛ ተራራዎች መካከል አንዱ የሆነው አሊቾ ውሪሮ ወረዳ ጠረጋና ምዕራብ አዘርነት ሙጎ አካባቢ ከባህር ጠለል በላይ ከፍተኛውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ ከዞኑ የቆዳ ስፋት ውስጥ 24.6% ደጋ፤ 73.76% ወይናደጋና 1.64% ውርጭ ነው፡፡ የዝናብ መጠኑ ሲታይ ከፍተኛው 1200 ሚሊ ሜትር ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ 801 ሚሊ ሜትርነው፡፡ አብዛኛው የዞኑ ክፍሎች ከየካቲት እስከ ሚያዚያ ወራት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ ሲሆኑ ከሰኔ አጋማሽ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ የመኸር ዝናብ ያገኛሉ፡፡ ከፍተኛው አማካኝ የሙቀት መጠን 22.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርስ ሲሆን ዝቅተኛው 10.1 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ መሆኑን የሜትርዎሎጂ ትንበያ ያመለክታል፡፡
በዞኑ ለመስኖና ለሌሎች ተግባራት ሊውሉ የሚችሉ ሐይቆች፤ወንዞችናምንጮች ይገኛሉ፡፡
ሐይቆች፡- የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ዓሣዎች የሚገኙበት አባያ/ጡፋ ሀይቅእና ሀረ-ሸይጣን ሀይቅ
ወንዞች፡- ዲጆ፤ ፉርፉሮ፤ ካሊድ፤ ቆንቃይ፤ ዌራ፤ ጋሮሬ፤ ቦቦዶ ወዘተ....
ምንጮች፡- ምንጮች፡-መጨረፋ፣ አብጀት፣ ሙሸሼ፣ ሸሻር፣ ወኪሌ፤ ደማላደባይቢራ፤ ቀረሶ፤ ወሊያ ስድስት፤ ጫንጮ፤ ጣሊቀሳ፤ አትፊድግ፤ ጉጉሶና አንጀሌ ወዘተ....
የስልጤ ዞን የህዝብ ቁጥር በ1999 ዓ.ም የተደረገውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ መነሻ በማድረግ በ2015ዓ/ም 1,280,222 እንደ ሚሆን ሲገመት ከዚህ ውስጥ ወንድ 625,884 ሴት 654,339 በአጠቃላይ የገጠር ነዋሪ 993,835 የከተማ ነዋሪ 286,387 እንደሚሆንም በፕሮጀክሽን ይገመታል፡፡
በቂ ጥናት ባይካሄድም በዞኑ በርካታ ማዕድናት የሚገኝ ሲሆን በተለይም በስልጢ ወረዳ ፖታሽየም እንዲሁም በአብዛኛው ወረዳዎች ለግንባታ የሚያገለግሉ ድንጋይ፤አሸዋ፤ቀይ አፈር በብዛት ጥቅም ላይ በመዋል ላይ ይገኛል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በአሊቾ ውሪሮ እንስላስ ችኩል ተራራ እና በላንፉሮና ዳሎቻ ድንበር የሚገኘው የባልጬ ተራራ ከፍተኛ እምቅ ጂኦ-ተርማል ሀይል እንዳለው የእትዮጵያ ጂኦሎጂ ጥናትና ምርምር ተቋም መረጃ ይጠቁማል፡፡
በዞኑ ለቱርስት መስህብነት የሚሆኑ ታሪካዊ ቦታዎች፤የተፈጥሮ ደኖች፤ሐይቆች፤ወንዞችና ፍል ውሃዎች እንዲሁም ታሪካዊ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ከነዚህም ውስጥ
የስልጤ ዞን ከመሀል ኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ የሆነና የሀገራችን መዲና ከሆነችው አዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ቀደም ሲል በነበሩ ስርዓታት ህዝባችን ለዘመናት የዘመናዊ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ሳይሆን የቆየና በዚሁ ዘመን በነበሩ 11 የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ይማሩ የነበሩት ተማሪዎችም የገዢ መደቡ ቤተሰቦችና አቅሙ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ልጆች ብቻ ነበሩ። በደርግ ዘመንም በትምህርቱ ዘርፍ ቀደምሲል ከነበረው የፊውዳሉ ስርዓት መሻሻል የነበረ ቢሆንም አቅርቦትና ተደራሽነቱ የህዝቡን የትምህርት ጥማት ችግር የማይቀርፍና ብዙዎቹ ቤት እንዲቀሩና እድሉንም ያገኙት ት/ቤት ለማግኘት ረጅም ርቀት በመጓዝ ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው ቆይተዋል።
ከዚህ አንጻር በስልጤ ዞን ምስረታ በፊት በ1993 ዓ.ም.መጨረሻ የነበሩ ትምህርት ቤቶች በቁጥር 55 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 04 የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ብቻ ይገኝ ነበር፡፡ በመጋቢት 23/1993 የዞኑን ምስረታ ተከትሎ ባሉ ዓመታት በትምህርት ልማትና ተደራሽነት ላይ በርካታ ለውጦች የተመዘገቡ ሲሆን በመንግስት በኩልም የሰው ሀይል ልማት ከልማቶች ሁሉ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ በመገንዘብ ትምህርት ባልደረሰባቸው ቦታዎች በማዳረስ የተማረ ዜጋን ለማፍራት በሚያደርገው ከፍተኛ ርብርብ ሂደት ስራ ወዳዱና ታታሪው የስልጤ ህዝብ ተሳትፎ የጎላ ነበር፡፡ በዚህም ቅድመ 1993 ከነበረው 55 የአንደኛ ደርጃ ትምህርት ቤት እስከ 2015 የትምህርት ዘመን መጨረሻ ድረስ 336 እና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ 41 ለማድረስ የተቻለ ሲሆኑ በጠቅላላው 377 የትምህርት ተቋማት ደርሷል፡፡ በተጨማሪም በሀገር ደረጃ በልዩ ሁኔታ ብቃት ያለው የተማረ የሰው ኃይል በስፋት ለማፍራት እስከ 8ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ባለው በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ገብተው የሚማሩበት የአይረንዚ ልዩ አዳሪ ት/ት ቤት በስልማ አማካኝነት በማቋቋም በሀገር ደረጃ አስደማሚ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን ማፍራት የጀመረ ሲሆን ለዚሁ አገልግሎት የሚውልም G+3 ባለ 18 የመማሪያ ህንፃ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለ ሲሆን የቤተ መፅሓፍት እና የቤተሙከራ፣ የተማሪዎች መመገቢያ ካፌ ህንፃ እና የተማሪዎች ማደሪያ 2 ብሎክ G+2 ዶርም ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ሌላው የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኃላ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ያልመጣለቸው ተማሪዎች የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆችንና የኢንዱስትሪያል ኮሌጆችን በማስፋፋት ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ በ2004 በዞናችን በወራቤ ከተማ አንድ የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ተገንብቶ የመማር ማስተማር ስራውን በመጀመር ለበርካታ ወጣቶች አዳዲስ የስራ መስክ እየፈጠረ ከመሆኑም ባለፈ ከ2011 ጀምሮ ወደ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እንዲያድግ ተደርጓል። በተመሳሳይም ከ2008 የትምህርት የትምህርት ዘመን ጀምሮ የዳሎቻ፣ የሳንኩራ፣ የምዕራብ አዘርነት፣ የአሊቾ-ውሪሮና የጦራ ከተማ የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጆች ተመስርተው በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በ2013 ምስ/አዘርነትና የቅበት ከተማ አዲስ የኮሌጅ ማስጀመሪያ ዕውቅና አግኝተው የማስተማር ስር ጀምረዋል፡፡ በድምሩ በዞኑ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ቁጥር 09 ደርሷል፡፡ እንዲሁም የሀገር አቀፍ የወራቤ ዩኒቨርሲቲም በ2007 ግንባታው ተጀምሮ ከ2009 ጀምሮ ስራውን የጀመረ በመሆኑ ለዘመናት ትምህርት ለተጠማው ለአካባቢው ማህበረሰብ ምቹ ሁኔታን በመፍጠሩ በዞኑ የሰው ሀይል ልማት ላይም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡
በ1993 የትምህርት ዘመን በአንደኛ ደረጃ 9887 ተማሪዎች በ55 ትምህርት ቤቶች ተመዝግበው እየተማሩ የነበሩ ሲሆን በ2015 የትምህርት ዘመን በ725 አፀደ ህጻናት ት/ቤትና ቅድመ-መደበኛ ጣቢያዎች 65,047 ተማሪዎችና በ41 2ኛ ደረጃ 43,287 ተማሪዎች እና 336 1ኛ ደረጃ የመንግስት በጠቅላላው 234,275 ተማሪዎች በ15 የግል ትምህርት ቤቶች 3,244 ተማሪዎችና164 አማራጭ መሰረታዊ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ቆይተዋል። የመጀመሪያ ደረጃ (1-8) ጥቅል የትምህርት ተሳትፎ ወንድ 88.45 ሴት 86.71 በድምሩ 87.59 ማድረስ ተችሏል፡፡የመጀመሪያ ደረጃ (1-8) ንጥር የትምህርት ተሳትፎ ወንድ 85.89 ሴት 84.27 በድምሩ 85.09 ማድረስ ተችሏል፡፡የሁለተኛ ደረጃ (9-10) ጥቅል የትምህርት ተሳትፎ ወንድ 38.32 ሴት 35.03 በድምሩ 36.63 ማድረስ ተችሏል፡፡ የ2ኛ ደረጃ (9-12) ንጥር ተሳትፎ ወንድ 36.01 ሴት 36.64 በድምሩ 36.33 ደርሷል፡፡በትምህርት ዘመኑ በየትምህርት እርከኑ በማስተማር ስራ ላይ የነበሩ መምህራን፣O ክፍል=ወንድ 186 ሴት 355 ድምር 541፤ 1-6ወንድ 2,229 ሴት 1,334 ድምር 3,563፣ 7-8 ወንድ 1,568 ሴት 422 ድምር 1,990 (1-8 ወንድ 3,797 ሴት 1,756 ድምር 5,553) 9-12 ወንድ 1,162 ሴት 244 ድምር 1,406 (በጠቅላላው ወ 5,145 ሴ 2,355 ድ 7,500 መምህራን አማካኝነት ትምህርት ተሰጥቷል፡፡
የጤና መሰረተ ልማት ከማስፋፋት አኳያ ከ1993 በፊት 11 ክሊኒኮች ብቻ አገልግሎት ይሰጡ የነበረ ሲሆን በ2015 የበጀት ዓመት መጨረሻ 181 ጤና ኬላዎች፣ 36 ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እንዲሰጡ የተደረገ ከመሆኑም በተጨማሪ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዞኑ አንድም ሆስፒታል ያልነበረው ሲሆን ከጤና ጣቢያዎች አቅም በላይ ለሆኑ ከፍተኛ ህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ቡታጂራ ሆስፒታል፣ ሆሳዕና ሆስፒታል፣ ኩየራ ሆስፒታል እና እንዲሁም አዲስ አበባ ሆስፒታሎች ከፍተኛ እርቀት በመጓዝ ይደርስ የነበረውን ከፍተኛ እንግልት ለማስቀረት መንግስትና የዞኑ ህብረተሰብ በመተባበር የወራቤ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን በመገንባት በህዳር ወር 2007 በይፋ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ አገልግሎት የመጀመሩ ፋይዳው ለዞኑ ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ዞኖችም ትልቅ የምስራች ሆኖ በመገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
የሆስፒታሉን መከፈት በወሊድ አገልግሎት ብቻ እንኳን ለውጡን ብንመለከት በየዓመቱ ይወልዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ እናቶች መካከል 15 በመቶ የሚሆኑት ከጤና ጣቢያ አቅም በላይ ሆኖ ለወሊድ ወደ ሆስፒታል ሪፈር ተብለው የሚላኩ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ እናቶች ሆስፒታል ወዳለበት በመሄድ ከመንገላታቸውም ባሻገር ለመሄድ ሳይዘጋጁ ቤታቸው ሊሞቱ የሚችሉ እናቶችም ቁጥሩ ቀላል አልነበረም፡፡ ከወራቤ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተጨማሪ ሶስት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ማለትም የቅበት ሆስፒታል፣ የዓለም ገበያ ሆስፒታል እና የጦራ ሆስፒታል ተጠናቀው ስራ የጀመሩ ሲሆን የቂልጦ ሆስፒታል ግንባታም እየተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሆስፒታሎችም ቁጥር ወደ አራት ከፍ በማለቱ የእናቶችንና የህፃናትን ሞት መቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ አሁን እስከ 2015 የበጀት አመት መጨረሻ ድረስ ባሉን 181 የጤና ኬላዎችና 36 የጤና ጣቢያዎች እና ስራ ላይ ያሉ 03 ሆስፒታሎችና በግንባታ ላይ ያለ 01 እና 01 ኮንፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንዲሁም ክሊኒክ 82 ተቋቁመው ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
የእናቶችና ህጻናትን ጤና አገልግሎቶችን አጠናክሮ መተግበር በሀገራችን የተጀመረውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንዲሁም የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በዞናችን እናቶችና ህፃናት ጤና ማሻሻል እንዲቻል ለጤና ልማት ሰራዊት ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በየደረጃው የተጠናከረ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡
የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ማስፋፋትና ማጠናከር ሀገራችን ካላት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር የተመጣጠነ የህዝብ ዕድገት እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ ለዜጎች የሥነ ተዋልዶ ጤና ሁኔታ መሻሸል ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይታመናል፡፡ስለሆነም የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚነት መጨመር በዋናነት የእናቶችንና የሕፃናትን የህመምና የሞት መጠን መቀነስ ይቻላል፡፡ስለዚህም የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶችን ከሚያስፈልጉ አማራጭ የቤተሰብ ምጣኔ ዘዴ ግብዓቶች ጋር ተጠቀሚዎች በሚመርጡትና በወሰኑት ዓይነት፤በፈለጉት ቦታና ጊዜ ተደራሽ በማድረግ የተጠቀሚዎችን ቁጥር መጨመር ወሳኝ አድርጎ በመውሰድ እየተሠራ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ባሳለፍነዉ 2015 በጀት ዓመት በመውለድ እድሜ ክልል ከሚገኙ ሴቶች በዞናችን አገልግሎቱን ለመስጠት ከታቀደው 231,298 ሴቶች ውስጥ 209101 በመዉለድ እድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ የተቸለ ሲሆን ሽፋኑ 90% ደርሷል፡፡ ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚታመሙና የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ የቅድመ ወሊድ፤የወሊድና ድህረ ወሊድ ጤና አገልግሎቶችን ተደራሽና ተጠቃሚ ማድረግ አስፈላጊና ወሳኝ በመሆኑ የጤናው ሴክተር ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በስፋት እየተሰራበት ይገኛል፡፡ከእነዚህም መካከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ፤የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን የማስፋፋት የማጠናከርና የግብዓት አቅርቦትን የማረጋገጥ እነዲሁም የባለሙያዎችን ክህሎት የማሻሻል ተግባራት ዋነኞቹ ናቸው፡፡በዚህም መሠረት እናቶች ወደ ጤና ተቋማትን መጥተው እንዲወልዱ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል፡፡እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጤና ጣቢያ መምጣት ላልቻሉት በአቅራቢያቸው በሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኛች አማካይነት አገልግሎቱን በጤና ኬላ ደረጃ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
የቅድመ ወሊድ ክትትል አገልግሎትን ማግኘት ከሚጠበቅባቸው ለ40,332 ነፍሰጡሮች መካከል 41,596 እናቶች አገልግሎቱን ቢያንስ አንድ ጊዜ ያገኙ ሲሆን ይህም አገልግሎቱን ማግኘት ከሚገባቸው እናቶች 103% ሆኗል፡፡
በጤና ተቋማት የሚሰጠውን የወሊድ አገልግሎትን ለ39,508 እናቶች በዞኑ በሚገኙ የጤና ተቋማት ውስጥ የወሊድ አገልግሎት እንድያገኙ የተደረገ ሲሆን ይህም አገልግሎቱን ማግኘት ከሚገባቸው እናቶች ቁጥር አንጻር ሽፋኑ 98% ማድረስ ተችሏል፡፡ ሁሉም በሰለጠኑ ጤና ባለሙያዎች /በጤና ጣቢያ/ ድጋፍ የወለዱ እናቶች ናቸው፡፡ ይህን ተግባር ከፍ ለማድረግ በዋናነት የሴቶች ልማት ቡድኖችን የማጠናከርና የአጠቃላይ ማህበረሰቡን ንቃት ማሳደግ እንዲሁም የጤና ተቋማት አቅምና ዝግጁነት ማጠናከር ያስፈልጋል::
የሳንባ ነቀርሳ በሽታ መከላከየ/ቢሲጂ/ ክትባት አገልግሎትን እድሜያቸው ከ1 አመት በታች ለሆኑ ለ43,676 ህፃናት ለመስጠት የተቻለ በመሆኑ ሽፋኑም አገልግሎቱን ማግኘት ከሚጠበቅባቸዉ ህፃናት ውስጥ 108% ይሆናል፡፡የፔንታቫለንት ሦስት ክትባትን ለ40,805 ህፃናት ለመስጠት የተቻለ ሲሆን ይህም አገልግሎቱን ማግኘት ከሚጠበቅባቸዉ ህፃናት አንፃር ሽፋኑ ከ110% ደርሷል፡፡ በተመሳሳይ የኩፍኝ በሽታ መከለከያ ክትባትን ለ39,556 ህፃናት ለመስጠት የተቻለ ሲሆን ይህም አገልግሎቱን ማግኘት ከሚጠበቅባቸዉ ህፃናት አንፃር ሽፋኑ ከ106% ሆኗል፡፡ እንዲሁም 38,595 ህፃናት ደግሞ ሁሉንም ክትባት ጨርሰው የወሰዱ በመሆኑ አገልግሎቱን ማግኘት ከሚጠበቅባቸዉ ህፃናት አንፃር ሽፋኑን ከ103.7% ማድረስ ተችሏል፡፡ የሳምባ ምች መከላከያ ክትባት ፒ.ሲ.ቪ ለ3ኛ ጊዜ 40,704 ህጻናት የተሰጠ ሲሆን አገልግሎቱን ማግኘት ከሚገባቸው ህጻናት መካከልም ሽፋኑ ከ103% መሆኑን ያመላክታል፡፡ የአካባቢ ቁጥጥር ከወባ መከላከል እና ቁጥጥር ዘዴዎች አንዱና በህብረተሰብ ተሳትፎ የሚከናወን ነው፡፡በ2015 በጀት ዓመት የአልጋ አጎበር ተጠቃሚዎች ብዛት 239763 መሆኑ ተራጋግጧል፡፡
የሀገራችንን ኢኮኖሚ ልማት በማሳደግ ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ እና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ከሚገኙ ቁልፍ የልማት ዘርፎች መካከል የግሉ ኢንቨስትመንት ልማት፣ የኢንተርፕራይዞች ልማት እና የንግዱ ዘርፎች በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የስልጤ ብሄረሰብም የሀገራችን ህገ-መንግስት ያረጋገጠለትን ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተጠቃሚ በመሆን በመጋቢት 23/1993 በተረጋገጠው የህዝበ-ውሳኔ መሠረት የስልጤ ዞን ተዋቅሮ ስራ ጀምሯል፡፡ ከዞናችን ምስረታ በኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተፈጠረውን ምቹ የልማት ሁኔታ በመጠቀም በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም በኢንቨስትመንት ዘርፉ እና በስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም የንግዱ ዘርፍ በመጠንም ሆነ በዓይነት ከዓመት ዓመት በከፍተኛ መጠን እያደገ መጥቷል፡፡ በሦስቱም ዘርፎች አብዛኞቹ ውጤታማ ከመሆናቸውም ባሻገር የዞናችንን ልማት ለማፋጠን በሚደረገው ርብርብ የድርሻቸውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡
የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በተለያዩ ክፍለ ኢኮኖሚዎች ተሰማርተው እንዲያለሙና ለልማታችን እድገት ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክቱ የሚያደርግ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲና ስትራቴጂ ተነድፎ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የግል ባለሀብቶች ወደ ዞናችን ገብተው እንዲያለሙ ለማስቻል፤ ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት በመከተል፣ የኢንቨስትመንት መሬት አዘጋጅቶ በመስጠት፣ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ፣ባዛርና ኤግዚቢሽን በየዓመቱ በማዘጋጀት የዞኑን የኢንቨስትመንት አቅምን በማስተዋወቅ፣ እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጭ ዕድሎችን በተለያዩ አማራጮች በማስተዋወቅ ሌሎችም ዘርፉን የሚመለከቱ በርካታ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በተደረገው ጥረትም ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ዞናችን የሚመጣው የባለሀብት ፍሰት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ የተፈጠረውን ሀገራዊ ምቹ ሁኔታ ተጠቅመን እንቅስቃሴ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ በዞናችን በግል ባለሀብቱ የልማት ተሳትፎ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል፡፡
ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በዞኑ በኢንድስትሪ ዘርፍ 191፣ በግብርና ዘርፍ 54 እና በአገልግሎት ዘርፍ 59 በአጠቃላይ 304 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 3,004,986,313 (ሶስት ቢሊዮን አራት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ስድስት ሺህ ሦስት መቶ አስራ ሶስት ብር) ካፒታል ያስመዘገቡ ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደዉ እየተንቀሳቀሱ ሲሆን ለ2303 ዜጎች በቋሚ እና 2,431 በጊዜያዊ በድምሩ ለ4,734 ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ ውስጥ 2015 በጀት አመት በዞኑ በምደባ እና በልዩ ጨረታ በኢንድስቱሪ 14፣ በግብርና 38 እና በአገልግሎት ዘርፍ 115 በአጠቃላይ 67 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ በማዉጣት ያስመዘገቡት ካፒታል በኢንዱስቱሪ 531,203,033 ብር፣በግብርና 285,965,232ብር በአገልግሎት 678,927,966ብር በድምሩ 1,496,096,231 ብር ካፒታል ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ አዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ ፕሮጀክቶች ለ 4,712 ቋሚ እና ለ 1,477 ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥሩ አስመዝግበዋል፡፡በአጠቃላይ በቅርብ አመታት የዞኑን የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጭ እድሎች እና ፖቴንሻል የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ይህንንም ተከትሎ የዞኑ ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለዚህም አብነት ማሳያ የሚሆን በ2015 በጀት አመት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች 492 በላይ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች በሁሉም መዋቅር መቅረቡ በቂ ማሳያ ነዉ፡፡
በከተሞች የሚታየውን ድህነት እና ስራ አጥነት በመሰረቱ ለመቀነስ እንዲያስችል የከተማ ልማት ፖሊሲ ተቀርጾ እየተሰራ ይገኛል፡፡ እንደ ዞናችን ይህ የልማት ፖሊሲ ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረበት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በዞኑ ከተሞች የነበረውን ድህነት እና ስራ አጥነት በመቀነስ ሂደት ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም በጥቃቅንና አነስተኛው ዘርፉ በዞናችን ከ1998- 2015 በጀት ዓመት ለ182,328 ያህል ዜጎች በተለያዩ ዘርፎች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡ከዚህ ውስጥ በ2015 የተፈጠረው የስራ ዕድል ፈጠራ ብዛት 30,213 ሲሆን በየዓመቱ የስራ እድል የሚፈጠርላቸው ዜጎች መጠን እያደገ መጥቷል፡፡ በሚከተለው የሠንጠረዥ መረጃ በዝርዝር ተመላክቷል፡፡
በንግዱ ዘርፍ በሁሉም የዞናችን አካባቢዎች የነጋዴዎች መጠን ከአመት አመት በከፍተኛ መጠን እያደገ የሚገኝ ነው፡፡ ለአብነትም ከ1994 ዓ.ም በፊት በዞናችን ይንቀሳቀሱ የነበሩ ህጋዊ ነጋዴዎች መጠን ከ200 በታች የነበረ ሲሆን በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ዛሬ ላይ በዞናችን የታደሰ የንግድ ፈቃድ ያላቸው ነጋዴዎች ቁጥር ከ11,546 ደርሷል፡፡ ስለሆነም ነጋዴዎች የነፃ ገበያ ስርዓትን ተከትለው ህብረተሰቡን በፍትሃዊነት እንዲያገለግሉ እየተደረገ ነው፡፡የዞኑን የንግድ ስርዓት ወደ ዘመናዊነት ከማሸጋገር አንፃር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን የዳታ ቤዝ ዝርጋታ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የዳታ ቤዝ የመረጃ ስርዓት በአሁኑ ሰዓት በሁሉም ወረዳዎች እና የወራቤ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ ማድረግ በሚያስችል ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡በቀጣይም በተለያዩ ዘርፎች የንግድ ልማታችን እንዲስፋፋ በማድረግ በዞኑ ጤናማ የሆነ የንግድ ስርዓት እንዲኖር መስራት ያስፈልጋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ የሀገራችን ዋነኛ የገቢ ምንጭ ከመሆኑም በላይ ከ80 በመቶ በላይ የሆነው የገጠሩ ህብረተሰብ መተዳደሪያ እንደሆነ የበርካታ የመረጃ ምንጮች እውነታ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዞናችንም በተመሳሳይ መልኩ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህብረተሰብ በግብርና ሥራ ማለትም በእርሻና በእንስሳት እርባታ ነው የሚተዳደረው፡፡ በመሆኑም የአካባቢውን የኑሮና የኢኮኖሚ ደረጃ ለማሻሻል የግብርናን ምርትና ምርታማነትን በሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮች ላይ ህብረተሰቡን በሰራዊት በማደራጀትና በማዝመት ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ የግድ የሚል ነው፡፡ በዚህም መሰረት ዞኑ ከተመሰረተበት ዕለት አንስቶ (ምንም እንኳን በመጀመሪያዎቹ ሁለትና ሶስት አመታት መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን በማጠናከር ላይ ያተኮረ ቢሆንም) ባደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል የተመዘገቡ አብነታዊ ውጤቶች እንደሚከተለው ለመጥቀስ ተሞክሮዋል፡፡ እነዚህም፡-
በ1993/94 በጀት አመት 34,250 የኤክስቴንሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ከነበረበት በ1994/95 በጀት አመት የኤክስቴንሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ወደ 39,000 አ/አደር ማሳደግ የተቻለ ሲሆን ይህም በ2014/15 ም/ዘመን ወደ 197,712 አ/አደሮች ማሳደግ ተችሏል፡፡ በዚህም የተመዘገበው ዋናው ውጤት ሲታይ በ1983 57,152 ሄ/ር የነበረው ዓመታዊ የሰብል መሬት ሽፋን በ1995/96 ም/ዘመን ወደ 107,439 ሄ/ር ያደገ ሲሆን ይህም በ2014/15 ወደ 165,027.27 ሄ/ር ማሳደግ ተችሏል፡፡ በምርት ረገድም በ1983/84 ም/ዘመን 648,675 ኩ/ል የነበረው አመታዊ ምርት በ1995/06 1,335,648 ኩ/ል ያደገ ሲሆን ይህንንም በ2014/15 ወደ 63,511,177 ኩ/ል ማድረስ ተችሏል፡፡ ምርትና ምርታማነትን በተመለከተ በ19983/84 በጥቅሉ የዞኑ የሰብል ምርታማነት 11.35 ኩ/ል በሄ/ር ከነበረበት በ1995/96 በጥቅሉ የዞኑ የሰብል ምርታማነት 12.43 ኩ/ል በሄ/ር ያደገ ሲሆን ይህም በ2014/15 ም/ዘመን በጥቅሉ የዞኑ የሰብል ምርታማነት 69.41 ኩ/ል በሄ/ር እንዳደገ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ከ1983 በጀት አመት ጀምሮ ምንም እንቅስቃሴ ካልነበረበት የመስኖ ልማት ስራ በ2000 በጀት አመት 3475 ሄ/ር መሬትና 815080 ኩ/ል ምርት ማሳካት የተቻለ ሲሆን ይህንንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጥፍ በማሳደግ በ2014/15 በጀት አመት በ1ኛ እና 2ኛ ዙር የመስኖ ልማት ከ13,075.795 ሄክታር እና 3,634,995.06 ኩንታል በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህ የምርት እድገት ሊመጣ የቻለው ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ግብዓት በማቅረብና በአጠቃቀሙ ዙሪያ የባለሙያ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ አ/አደሩን በክህሎት ለማነጽ በአቅራቢያ የገበሬ ማሠልጠኛ ማዕከላት በመገንባት በወቅታዊ ሥራዎች ስልጠና በመስጠት እንዲሁም ብዙ ሞዴሎችን ለማፍራት አርሶ አደሩን በማትጋትና በመሸለም ተከታታይነት ያለውን ስራ በመሰራቱ ነው፡፡
አ/አደሩ ከባለሙያው ከሚሰጠው ምክርና ድጋፍ ባሻገር እንዴት ግብርናን ዘመናዊ በሆነ መልኩ አቀናጅቶ በሚፈለገው ደረጃ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አልፎ በገቢ ምንጭነት በመጠቀም ወደ ባለሀብትነት መሸጋገር እንደሚቻል አ/አደሩ በአይኑ በራሱ መሬትና በራሱ አካባቢ መማር እንዲችል የገበሬ ማሰልጠኛ ማዕከላት ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ ስለሆነም ይህንን ከግብ ለማድረስ በ1993 በጀት አመት ምንም ካልነበረበት በ1997 በጀት አመት 36 ማድረስ የተቻለ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በዞኑ ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች አንድና ከአንድ በላይ ገማማ በማቋቋም በዞን ደረጃ ወደ 179 ገመማዎች ተገንብተው በሰርቶ ማሳያ ቦታዎች በተግባር የታገዘ ልማታዊ ተግባር በማከናወን ላይ ናቸው፡፡
ዞኑ ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት ሀብት ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ዘርፉን ውጤታማ የሚያደርጉና የአረሶ-አደሩን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ በመሆኑ በእንስሳቱና የእንስሳት ውጤቶች አርሶ አደሮች በተሻለ ደረጃ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡ በዘርፉ ባለፉት ዓመታት በተደረገ እንቅስቃሴ በወተት ምርት ማሻሻያ፣ በስጋ ምርት ማሻሻያ፣ በዶሮ እንቁላልና ስጋ ምርት ማሻሻያ፣ በማርና ሰም ልማት፣ በዓሳ ሀብት ልማት፣ በመኖ ልማትና በእንስሳት ጤና አገልግሎቶችን በላቀ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህም መሰረት የሰው ሰራሽ ማዳቀል አገልግሎት በ1993 በጀት አመት ምንም እንቅስቃሴ ካልነበረበት በ1999 በጀት አመት ከነበረበት 1214 ላሞችን በተሻሻለ ኮርማ ዝርያን የማሻሻል ስራ የተሰራ ሲሆን ይህንንም ቁጥር በ2004 በጀት አመት ወደ 6980 ላሞች ማድረስ የተቻለ ሲሆን በ2007 በጀት አመትም በተሻለ መልኩ እንቅስቃሴ በማድረግ 22789 ላሞች በሲንክሮናይዜሽን፣ በ2014 ዓ.ም 27,761 በመደበኛና በተሻሻለ ኮርማ ዝርያቸው እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ በዚህም በ1993 በጀት ዓመት የወተት ምርት በጣም ውስን ከነበረበት በ2002 ከነበረበት 12200 ቶን፤ በ2007 በጀት ዓመት 43059 ቶን በ2014 ዓመት ወደ 63,729 ቶን ማድረስ ተችሏል፡፡
ለተጨማሪና ዝርዝር መረጃ ከታችት ያለውን ፋይል ያውርዱ!
Silte_Silte zone data.pdf