
ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ያጎናፀፈውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለስልጤ ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የዞኑ ብልፅግና ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ነዒማ ሙኒር ተናገሩ።
በዞኑ ለተመዘገቡ ውጤቶች እውቅና ከመስጠት ባሻገር ጥንካሬዎችን ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
መጋቢት 23 ቀን 1993 ዓ.ም የስልጤ ብሔረሰብ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት በህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ መሰረት ምላሽ ያገኘበት ዕለት በየዓመቱ እየተከበረ ዘንድሮ 24ኛ ዓመት ላይ መድረሱን የገለፁት የስልጤ ዞን ብልፅግና ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ነዒማ ሙኒር፥ የረዥም ጊዜ ጥያቄ የነበረው የማንነት ጥያቄ የተመለሰበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የስልጤ ህዝብ የራሱን አስተዳደር መዋቅር መስርቶ በአጎራባች ዞኖች በተለያዩ የአስተዳደር መዋቅሮች ይተዳደሩ የነበሩ የስልጤ ብሔረሰብን በአንድ ዞናዊ መዋቅር እንዲሰባሰቡ ያስቻለ መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ነዒማ፥ የማንነት መገለጫ የሆኑት ባህሉን፣ ቋንቋ፣ ታሪኩንና ትውፊቶቹን ከማሳደግ ባሻገር በሃገሪቱ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ሌሎችም መስኮች የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።
ባለፉት አመታት ለተመዘገቡ ውጤቶችና ለተደረጉ ጥረቶች በቂ እውቅና መስጠት እና ጥንካሬዎችን ማስቀጠል እንደሚገባም አክለዋል።
ያመለጡ ዕድሎችን ፈትሾ በቂ ትምህርት መውሰድ እና ስህተቶችን ማረም አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት የስልጤ ዞን ብልፅግና ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ነዒማ ሙኒር፥ ወቅቱን የዋጀ የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ስራ መከወን ከሁላችንም ይጠበቃል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከመቼውም በላይ አብሮነትን በማጠናከር ለሃገራችን ብልፅግና በጋራ መትጋት ይገባናል በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል ሲል የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዘግቧል።
አስተያየትዎን ይጻፉልን