የስልጤ ብሄር በህልና እሴት

ቋንቋ

የስልጤ ብሔረሰብ አፍ መፍቻ ቋንቋ ስልጢኛ ሲሆን ከሴማዊ የቋንቋ ቤተሰብ ይመደባል፡፡ ቋንቋው ከአረብኛ፣ ከጉራጊኛ ፣ ከሐረሪ፣ ቋንቋዎች ጋር ይመሳሰላል፡፡ የብሔረሰቡ አባላት ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ በከተሞች አካባቢ ያሉ አማርኛን እንዲሁም እንደ አጐራባችነታቸውና ቅርበታቸው የሀድይኛ፣ የማረቆኛ፣ የጉራግኛ፣ የኦሮምኛ እና የሀላብኛን ቋንቋዎች በሁለተኛ ደረጃ ይናገራሉ፡፡ ሌሎችም አጐራባች ብሔረሰቦች እንዲሁ የስልጢኛን ቋንቋ እንደየቅርበታቸው ለመግባቢያነት ይጠቀማሉ፡፡

ስልጢኛ ከ60 ዓመት በፊት የአረብኛ ፊደልን በመጠቀም ለጽሑፍ የዋለ ቋንቋ ቢሆንም ከ1967 ዓ/ም ጀምሮ ልዩ ልዩ አዋጆች እና የመሰረተ ትምህርት ማስተማሪያ መጽሐፍት የሳባ ፊደልን በመጠቀም በቋንቋው ተተርጉመዋል፡፡ ከ1987 ዓ/ም ጀምሮ የ1ኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሣይክል የመማሪያ መጽሐፍት በቋንቋው ተዘጋጅተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የትምህርት ቋንቋ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ እንደዚሁም የሣባ ፊደልን በመጠቀም የመማሪያ መጽሐፍት፣ የስልጢኛ መዝገበ ቃላት፣ የስልጤ ሕዝብ ታሪክ እና ሌሎች መጽሀፍቶች በቋንቋው ተጽፈው አገልግሎት እየሠጡ መሆናቸው ቋንቋው በማደግ ላይ ያለ ስለሚሆኑ የሚገልፁ እውነታዎች ናቸው፡፡

የስልጤ ባህል

ባህላዊ አስተዳደር

በስልጤ ብሔረሰብ ውስጥ በርካታ ማህበራዊ ቡድኖች / ጐሣዎች/ ያሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ስልጤ፣ መልጋ፣ ችሮ ፣ ዲላባ/ጳ/፣ ኑግሶ /ኦግሶ/፣ አሊቶ፣ አባሮ፣ ኡራጎ፣ ጉምቢ፣ ጊዳዋሁሴንና አለቂሮ ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ እያንዳንዳቸው በንዑሣን ጐሣዎች የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ ከላይ የተገለኒትንም ሆነ ሌሎችንም ጐሣዎች በአንድ ላይ የሚያስተሳስርና የሚያስተዳድር "ጐጐት" የሚባል ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት ያላቸው ሲሆን የሥርዐቱ አፈፃፀም "ሴራ" ወይንም "ዳምቡስ" በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት የሚመራው በጐሣ መሪዎች ሲሆን እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ የሥልጣን ተዋረድ እና ህጋዊ መተዳደሪያ ደንብ አላቸው፡፡

የብሐረሰቡ ባህላዊ አስተዳደር የተለያዩ የስልጣን ሀላፊነትና የሥራ ድርሻ ያላቸውን አካላት ያቀፈ ሲሆን በዚህ የስልጣን ተዋረድ መሰረት "ገራድ" ዋና ዳኛ ሲሆን ከዚህ በታች ሙሉ ገራድ፣ ወላብግራድ፣ ሣረ ገራድ በመባል የሚታወቁ ረዳቶች አሉት፡፡ ከነዚህ ባህላዊ አስተዳደር አካላት በተጨማሪ የበታች አስተዳደር የሚባሉ "ሞሮ" የጐሣ ተጠሪ፣ ሙራ" የአካባቢ ተጠሪና ተላላኪ፣ እና በቤተሰብ ደረጃ የቤተሰብ ሸንጐ የሚባሉ አሉ፡፡ እያንዳንዱ ጐሣ "ሜልቾ" የሚባል ጉባኤ አለው፡፡ ከዚህም ባሻገር በብሔረሰቡ ዘንድ አራት ደረጃ ያሉት ባህላዊ የፍትህ ሥርዓት ያለ ሲሆን እነዚህም እንደየቅደም ተከተላቸው እና የሥራ ተግባራቸው "ማገ" ፣ “ራጋ" /ህግ ተርጓሚ/፣ ፈርዛገኝ /ይግባኝ ሰጪ ክፍል/ እና "ወገጋገኜ" በመባል ይጠራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት በብሔረሰቡ ውስጥ የሚከሠቱ ግጭቶችንና ወንጀሎችን እንደየክብደታቸው እና ጥፋታቸው መጠን በመመዘን ተገቢውን ቅጣት በመስጠት በባህላዊ መንገድ ግጭት የሚፈታበት አካሄድ አለው፡፡

አንድ የማህበረሰቡ አባል የነፍስ ማጥፋት ወንጀል ቢፈጸም ወንጀሉን አውቆና አስቦበት አሊያም በድንገት የፈፀመ መሆን እለመሆኑን በማጣራትና በመመርመር በባህላዊ መንገድ ፍርድ ይሠጣል፡፡ ይህም በብሔረሰቡ አጋርሳ፣ ተተጋ፣ ሰበባ፣ ተልካና ተልማ በማለት እንደወንጀሎቹ ዓይነት ቅጣት ይቀጣሉ፡፡ በሥርዓቱ "ሙሊ" በሚባል የመሐላ እና የወንጀል ምርመራ ጥበብ ድብቅ ወንጀሎች ይወጣጣሉ፡፡ የተጠርጣሪው ወንጀለኛ የወንድና የሴት አያት ወገኖች አብረው መሀላ እንደፈጽሙ ይደረጋል፡፡ ይህን ለመፈፀም ፈቃደኛ ካልሆነ ተጠርጣሪው በወንጀለኛነት ይፈረጃል፡፡ በተለይ የነፍስ ማጥፋት ወንጀል የፈፀመ መሆኑ ከተረጋገጠ የወንጀለኛው ወገኖች ካሣ ይከፍላሉ፡፡

ሴቶች በባህላዊ ሥርዓቱ የመሰብሰብ መብት የላቸውም፡፡ በቤተሰብ እና ከአካባቢው ሕዝብ ጋር አለመስማማት ወይም አለመግባባት ሲፈጠር ግን ሴቶች ለሸንጎው "አቤት" ይላሉ፡፡ አቤቱታቸው ተሰሚነት ስላለው ፈጣን ምላሽ ያገኛሉ፡፡ በብሔረሰቡ ዘንድ የጎሣ መሪው ሚስት “ኢቲኮ” የሚል የማዕረግ ስም ይሠጣታል፡፡ እሱ ሥልጣኑን ሲረከብ ቤተሰቧቿ ከ50-60 ከብቶች በማምጣት ድግስ ደግሠው እሷንም ለማዕረጓ ተስማሚ የሆነ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ ሴቶች በኢኮኖሚው እና በሌሎችም ሥራዎች የጎላ ሚና አላቸው፡፡ አብዛኛው ስራ በብሔረሰቡ በሴቶች ጉልበት ይከናወናል፡፡

ባህላዊ እሴቶች

የጋብቻ ሥርዓት

በብሔረሰቡ ዘንድ ብዙ የጋብቻ ሥርዓት አይነቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያው በስፋት የተለመደው የስምምነት ጋብቻ ነው፡፡ ይህ የጋብቻ አይነት የአግቢው ቤተሰብ ሽማግሌ ወደ ልጅቷ ቤተሰቦች በመላክ በተገቢዎች ቤተሰብ ሥምምነት የሚፈፀም ነው፡፡ ሁለተኛው የጋብቻ ዓይነት "ኩል" ይባላል፡፡ በዚህ የጋብቻ ሥርዓት ልጅቱም ሆነች ቤተሰቦቿ ሣያውቁ አግቢው ፈረስ ላይ ተቀምጦ ከነፈረሱ ወደ ልጅቱ ቤት በመግባት አለንጋውን በቤቱ ምሰሶ ላይ አስሮ ልጅቱ እንድትሰጠው ቤተሰቧን የሚያስገድድበት ነው፡፡

ሶስተኛው በድሮ ግዜ የነበረ ነገርግን በአሁን ግዜ የሌለ/የጠፋ የጋብቻ ዓይነት “ጠለፋ”፡- ሲሆን ወላጅ ከላይ የተጠቀሰውን የኩል የጋብቻን ካልተቀበለ ልጅቱ ወይም ቤተሰቦቿ ልጅን ካልፈለጉ ወይም አግቢው ወጪና ጋጋታን በመፍራት የሚወስደው ሌላ አማራጭ ነው፡፡ በዚህም ልጅቱን ይዞ በመኮብለል በመጨረሻም ሽማግሌ ልኮ ጋብቻው የሚፈፀምበት ሥርዓት ነው፡፡ አራተኛው የጋብቻ ዓይነት “ኦጋ” የሚባል ሲሆን በዚህ የጋብቻ ሥርዓት ሴቷ የመረጠችው ልጅ አባት ቤት ሰተት ብላ በመግባት ምሰሶ ላይ ቅቤ ቀብታ እንዲያገባት የምትጠይቅበት ሥርዓት ነው፡፡ አምስተኛው የጋብቻ ዓይነት የውርስ ጋብቻ የሚባል ሲሆን በዚህ የጋብቻ ሥርዓት ባል ሲሞት የሟች ታላቅ ወይም ታናሽ ወንድም አለያም የቅርብ ዘመድ የሟችን ሚስት የሚያገባበት ወይም የሚወርስበት ሥርዓት ነው፡፡

በብሔረሰቡ ዘንድ ሠርግ እና የጥሎሽ ሥርዓት የሚፈፀመው እንደ ቤተሰቡ ኢኮኖሚ አቅም ነው፡፡ ብር ከሣር ጋር ተጨብጦ ለእናት፣ለአባትና ለቅርብ ዘመዷቿ ጉልበት እየተሳመ ይሰጣል፡፡ በስልጤ ብሔረሰብ ጋብቻ አፈፃፀም ብዙ ወጪ ያለባቸው የልጅቷ ወገኖች ናቸው፡፡ ለመተዳደሪያ እና ለመቋቋሚያ የሚሆን ቁሳቁስ እና ገንዘብ ቤተሰቦቿ ይደጉሟታል፡፡ በቅሎ መውረጃና የመቀነት መፍቻ ተብሎ የልጅቷ አባትና እህቶች ከብት ወይም ገንዘብ ለሙሽራዋ ይሸልማሉ፡፡ ሠርገኛዉ ወደ ሙሽሪት ቤት ከመሄዱ በፊት “አታካኖ” የሚባል ባህላዊ ምግብ ይመገባሉ፡፡ ልጅቱ ቤት ሠርገኞቹ ቅቤ እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ በሠርጉ ዕለት የሩቅና የቅርብ ዘመድ አዝማድ ይሰበሰባል፤ ከበሮ እየተደለቀ ይዘፈናል፡፡ ሙሽሪትን በቀን ብርሃን ይዞ መውጣት በባህሉ የተከለከለ ነው፡፡ ከጋብቻ በፊት የሴትና የወንድ ልጆች ግርዛት የተለመደ ሲሆን ሴቶች በወሊድ ወቅት ልዩ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡

ባህላዊ በዓላት

በብሔሰቡ ባህላዊ እና መንፈሳዊ በአላት ይከበራሉ፡፡ አረፋ እና ረመዳን ፆም ፍቺ እንዲሁም “ሸዋል” በሚባሉ ወቅቶች ህዝቡ በደማቅ ሁኔታ በዓላቱን ያከብራቸዋል፡፡

ባህላዊ የቤት አሠራር

በስልጤ ብሀሄረሰብ ባህላዊ የቤት አሠራር ብሔረሰቡን የቤት አሠራር ስንመለከት በደጋው የህብረተሰብ አጠረር " ገር " ማለት ቤት ስሆን ‹‹ጉዬ›› የሚባል ትልቅ ቤት ሲሆን ትንሹ" ዛገር'' ይበላል። በጥድ፣በባህር ዛፍና በቀርቀሀ ይሠራል፡፡ አንድ ሆኖ በትንሹ የሚሰራው ቤት ‹‹ጋር›› ሲባል መለስተኛ መጠን ያለው ሆኖ በቆላማው ክፍል ደግሞ ብዙ እንጨትና ሳር የማይፈልጉ የሣር ቤቶች ይሠራሉ፡፡ በነዚህ አካባቢዎች ሁሉም ቤቶች ግድግዳቸው በጭቃ ይለሰናል፡፡

ባህላዊ መሣሪያዎች

የሥልጤ ባህላዊ ቤትባህላዊ መሣሪያዎች በዕደ ጥበባት ሥራዎች በኩል ከሸክላ፣ከብረታ ብረት(ማረሻ)፣ከሻማ ስራ አልባሳት፣ከእንጨት ከቀርከሀ እና ከስንደዶ የተለያዩ የመገልገያ ዕቃዎች፣ መጠጫዎችና ጌጣጌጦች፣ ወለል ምጣፎችና የመኝታ ቁሳቁሶች በህዝቡ ዘንድ በግልና በህብረት ይመረታሉ፡፡ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ከሸንበቆ፣ከመቃ እንዲሁም ከብረትየትንፋሽ መሣሪያዎች ከቆዳ ደግሞ ከበሮን በመስራት ለሠርግ፣ ለአመታዊ ባህላዊ በዓላትና ለጭፈራ ይጠቀምባቸዋል፡፡ የጦር መሳሪያዎች እንደጋሻ፣ጦር፣ወስፈንጥርእንዲሁም አሽግሌ የተባሉትን በመጠቀም ምርቱን የሚያበላሹባቸውን አውሬዎች ለማጥመድና ለውጊያ ሲገለገልባቸው ኖሯል።

ባህላዊ ምግብና የአመጋገብ ሥርዓት

ብሔረሰቡ በበዓላት ጊዜ የሚያዘጋጃቸው ባህላዊ ምግቦች ሱልሶ(ክትፎ)፣ አተካኖ፣ አይብና ጎመን፣ የጎመን ክትፎ፣(ጨበሮ)፣ በቅቤ የታሸ ቆሎ (ሀና ቃላ) ይባላል፡፡ እንዲሁም ሻሜታ ይጠጣል፡፡ ቆጮ፣ ጦሮሾና በቆላማ ክፍል ደግሞ እንጀራ በአዘቦት ቀናት ይበላሉ፡፡

ባህላዊ የለቅሶ ስርዓት

ብሔረሰቡ የተለያዩ የለቅሶ ሥርአቶች አሉት፡፡ ትልቅ ሰው ወይም የሀገር ሽማግሌ ሲሞት መልዕክተኛ በተለያየ አቅጣጫ ይላካል፡፡ ፈረሰኛ ከጎረቤት ይመጣል፡፡ ሴቶች እንደየቅርበታቸው መሬት ላይ በመውደቅ ሀዘናቸውን ይገልፃሉ፡፡ የሟች ልብሶች ተይዘው ለቅሶ ይለቀሳል፡፡ ሟች የጎሣ መሪ ከሆነ ከቀብር በኋላ መሪነቱ ለልጅ ይሰጣል፡፡ ወራሹ ህፃን ከሆነ ሞግዚት ይመደብለታል፡፡ ትዳር ሳይመሰርት ለሞተ መሪር ሀዘን ይታዘናል፡፡

በዞኑ በርካታ ድንቅ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ቅርሶችና መስህቦች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል በኢትዮጵያ ጥናትና ቅርስ ጥበቃ የታወቀው የአሳኖ ተክል ድንጋይ ዋነኛው ሲሆን ሌሎችም የትክል ድንጋዩች በአልቾ ወረዳ ቃዋቆቶ ጣንዣ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የአይናጌ፣የኡርባ ዋሻዎችም እንዲሁ ታሪካዊ ናቸው ፡፡ ለሞሮ ፋፍፍሮ፣ወይራ የተባሉ ፏፏቴዎችና አሹቴ ሙቅ ውሃ፣ የቡራቆ፣ የሀሮ ሻይጣንና ትንሹ አባያ የተባሉ የተፈጥሮ ሃይቆች በዞኑ ሲገኙ ጋሮራ፣ዌራ፣ዲጆ፣ የተባሉ ወንዞችና ጋፋት፣ሙጎ፣ባልጨኩ ተራራዎችም እንዲሁ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ የሐጂ አሊዬ ኡምናን፣ አልኪ፣ጌስቴይ ጣሂራት፣ገንሠልጤ የተባሉ ጥንታዊ መስጊዶችም ከብሔረሰቡ ታሪካዊ ቅርሶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ለበላጣ መረጃ ቀጥሎ የላውን ኣንብቡ---