የስልጤ ህዝብ ታሪክ በከፊል

የስልጤ ህዝብ ታሪክ ከጅምር እስካሁን ያለዉን በሚያሳይ ደረጃ ተጽፎ የተደራጀ ባይሆንም ከሀጅአልዬ ዑመር አመጣጥ ጋር የሚተሳሰር ሲሆን ሐጂ አልዬ የሚባሉት የሀይማኖት መሪ ከበርበር ተነስተው በሐረር አድርገው ወደ መሀል ሀገር ከዚያም ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በርካታ የሀይማኖት ሰዎችን አስከትለው ከመጡ በኋላ ቀደም ብሎ በአካባቢው ይኖሩ ከነበሩት የ”ዥራ” ጎሳዎች መካከል አንዷን በማግባት አንድ ሴትና አምስት ወንድ ልጆችን እንደወለዱ እና እነሱም አዘርነት በርበሬ፣ ስልጢ፣ ሁልባረግ፣ አልቾ፣ ሳንኩረ፣ዳሎቻ፣ወለኔ፣ገደባኖ…ሌሎችም የስልጥኛ ተናጋሪ አካባቢዎች እንደተሰራጩ የዘርፉ ጻሀፊዎች ያብራራሉ፡፡ ሌላው የስልጤ አመጣጥ ጋር በተያያዘ ስልጤ የሚለው መተሪያ በታሪክ ተሰንዶ የተገኘው በ14ኛው ክፍለ ዘመን ንጉስ አምደ-ጽዮን ዘመነ መንግስት ነው ሲሉ የታሪክ አዋቂዎች ያስረዳሉ፡፡ በአጠቃላይ የስልጤ ህዝብ ታሪክ ከበርካታ የሀገራችን ህዝቦች ታሪካዊ ትስስር ያለው ሲሆን በደም፣ በጋብቻ፣ በሰፈራ፣ በንግድ ግንኙነት የተፈጠረና የጎለበተ እንደሆነ ከታሪክ ድርሳናት መገገንዛብ ተችሏል፡፡

የስልጤ ህዝብ በሀርላ፣ በዜይላ፣በባሌ፣በሸዋ…….ሙስሊም ሱልታኔቶች ምስረታና አደረጃጀት የራሱ አበርክቶና ተሳትፎ እንደነበረው ይነገራል፡፡ይህ የሚያሳየው ከ10 ክፍለ ዘመን በፊት ስልጥና ተናጋሪው የስልጤ ህዝብ ተመስርቷል ማለት ነው፡፡

እንደ ብራውካምፐር ገለፃ በሰሜኑ የሀዲያ ሱልጣኔት ሠፍረው የነበሩ የስልጤ ፣ የቀቤናና የሀላባ ህዝቦችም ከደቡብና ምስራቅ የሀገሪቷ ክፍል በመነሳት አሁኑ ያሉበት አካባቢ ሰፍረዋል (Braukämper 2001 ፡55፡56)፡፡ የስልጤ ህዝብም በአካባቢው የሰልጢኛ ቋንቋን ይናገሩ ከነበሩ ነባር ህዝቦች (ያፈር ሰብ ) ጋር በመቀላቀል አሁን ያለውን ህዝብ ሊፈጥር ችሏል፡፡ በዚህ ረጅም የታሪክ ሂደትና እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ህዝቦች ባጠቃላይ የስልጤ ህዝብ ከሌሎች እርስ በርስ የጋብቻ፣ የንግድ፣ የባህልና የመልክአምድር ትስስርና አንድነት ፈጥረዋል፡፡ የአገሪቷ ህዝቦችም በደም፣ በባህል፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ጠንካራ ትስስር ፈጠረዋል፡፡ የስልጤ ህዝብ በዙሪያው ከሚገኙ የጉራጌ፣ የማረቆና የኦሮሞ ህዝቦች ጋር በባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት የጋራ ችግሩን ሲፈታ ኖሯል፡ እየፈታም ይገኛል፡፡

የስልጤ ህዝብ ከተለያዩ ህዝቦች ያለው ታሪካዊ ትስስር

የስልጤ ህዝብ ከደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር በጋራ ያዳበራቸው የተለያዩ የጋራ እሴቶች አሉት፡፡ ህዝቡ በጥንታዊው የሀዲያ መንግስት ከሲዳማ፣ ሀዲያና የሀላባ ህዝቦች ጋር በጋራ የኖረ ሲሆን በተለይ ከሲዳማ ህዝብ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንደነበረው የአካባቢው ባህልና ታሪክ አዋቂዎች በስፋት ይናገራሉ፡፡ በስልጤ ህዝብ በስፋት ሰፍሮ የሚገኘውና ዥራ ተብሎ የሚታወቀው የስልጤ ማህበረሰብ ከሲዳማ ህዝብ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚገለፅ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ የሲዳማ ተወላጆች በተለያዩ የስልጤ አካባቢዎች የቁርአን ትምህርት ተምረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከ16ኛው ክ/ዘመን ማብቂያ ጀምሮ የስልጤ ገዥ መደቦች ከከምባታ የገዥ መደብ ጋር ጠንካራ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትስስር ከመፍጠራቸውም በተጨማሪ በጋብቻ ይተሳሰሩ እንደነበር በስፋት ይገለፃል፡፡ በዚህ ረገድ የሀጂ አልዬ ኡመር ልጅ የነበረችው ኦየታ ለከምባታ ንጉስ ሀመልማል ተድራ በኃላ በከምባታ ህዝብ ታዋቂ ለነበረው የኦየታ ሥርወ መንግስት መፈጠር መሠረት ሆናለች፡፡ የስልጤ ህዝብ ጋር ድንበር ብቻ ሳይሆን በጥንቱ የሃዲያ ሱልጣኔት በጋራ ኖረዋል፡፡ ግጭት በማስወገድና በተለያዩ ማህበራዊና ባህላዊ ዘርፎችም ጠንካራ የጋራ እሴትን አዳብረዋል፡፡ የፈረዛገኘ የዳኝነት ሥርዓት የስልጤና የጉራጌ ህዝቦች የጋራ ችግራቸውን በአንድነት የሚፈቱበት ሲሆን የስልጤና የማረቆ ህዝቦችም በራጋ ሥርዓት ግጭትን እየፈቱ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የስልጤ ሀዝብ ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ሥላለው መስተጋብርና አንድነት ከታች ቀርቧል፡፡

የስልጤና የኦሮሞ ህዝቦች ትስስር በተመለከተ፡ አደምነት ዩለይ ስልጤነት ኤለይ

እንደ ኘሮፌሰር ብራውካምፐር (2001፡55) የስልጤ ህዝብ ከ16ኛው ክ/ዘመን በፊት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ በአርሲ፣ በጅጅጋ፣ በሸርካ ገደብ፣ በጨርጨር ኮረብታና በባሌ አካባቢዎች ይኖር ነበር፡፡ ከ16ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ በተደረጉ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ህዝቡ አሁን ወደአለበት አካባቢ ሲመጣ በጥንቱ መኖሪያው የቀሩ የስልጤ ህዝቦች ከኦሮሞ ህዝቦች ጋር በጋብቻ ተዋህደው መስተጋብር በመፍጠር በሁለቱ ህዝቦች መካከል የባህል የማህበራዊና የታሪክ ግንኙነት እንዲፈጠር መሠረት ሆነ ፡፡

ብራውካምፐር/2001፣ 66/ እንዲህ ይላሉ “Those groups which can be identified as Hadiyya, both Cushitic and Semitic speaking maintained consciousness of related clans among various Oromo tribes, especially the Arsi, Gujji, Gile, Karrayyu and lttu. Just to mention one example the Adari clans in Arsi have Kept a marriage restriction with the East Gurage (Siltie) because they consider these people as their own kinsfolk and so claim of have spoken their Semitic language up to five genreation ago …”

“ እነዚህ ሴማዊም ሆኑ ኩሻዊ የሆኑ በጥንቱ ሀዲያ ይኖሩ የነበሩ ህዝቦች ከተለያዩ የኦሮሞ ጎሳዎች ጋር በተለይም ከአርሲ፣ ከጉጂ፣ ጊሌ ፣ ከረዮና ኢቱ ጋር ስላላቸው መስተጋብርና አንድነት ጥልቅ ግንዛቤ አላቸው ፡፡ ለምሳሌ አደሬ የሚባለው የአርሲ ኦሮሞ ጎሳ ከምስራቅ ጉራጌ ተናጋሪ /ስልጤ/ ህዝብ ጋር የጋብቻ ትስስርን ይከለክላል፡፡ ምክንያቱም የአርሲ አደሬዎች የስልጢኛን ቋንቋ ከአምስት ትውልድ በፊት ይናገሩ እንደነበሩና አንድ እንደሆኑም ስለሚያምኑ ነው፡፡” በማለት ምሁሩ ያብራራሉ ፡፡

በሌላ በኩል ከአገር ሽማግሌዎች የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የሀጅ አልዬ ልጅ ከሆኑት ገንስልጤ የምትወለደው ወሰኑቴ በአርሲ ኦሮሞ ታዋቂ የነበሩትን የሀጅ ነስረዲን ሸህ እድሪስን ልጅ ሽህ አደምን አግብታ ሰባት ልጆችን ወልዳለች ፡፡

ከነዚህ ውስጥ አዝማ ደንበል ደንበል ለተባለው የአርሲ ኦሮሞ ትልቅ ጐሳ መፈጠር ምክንያት በመሆን ለሁለቱ ህዝቦች ግንኙነትና ትስስር መሠረት ሆኗል፡፡ ወሰኑቴ ወደ ስልጤ ከልጆቿ ጋር በመመለስ ስድስቱ ልጆቿ ከስልጤ ጋር በጋብቻ ተሳስረው አደሙዬ ተብሎ ለሚታወቁ በርካታ ጎሳዎች መፈጠር ምክንያት ሆኑ፡፡ በዚህ ታሪካዊ የደም ትስስር የተፈጠሩት የደምበልና አደሙዬ ጎሳዎች በኦሮሚያ ክልል በባቱ (ዝዋይ) ፣ በአርሲ ነጌሌ ፣ ድጆ ኮምበል ኩየራ፣ ሻሸመኔ እና ቡልቡላ በስልጤ ዞን ደግሞ ላንፍሮና ዳሎቻ ወረዳዎች ይኖራሉ፡፡

ከዚህ ትስስር በመነጨ በርካታ ቁጥር ያላቸው የስልጤ ተወላጆች በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እስልምናን ለማስተማርና ለንግድ ከኦሮሞ ህዝቦች ጋር ተዋህደው የሚኖሩ ሲሆን በአጎራባች አካባቢዎች የድንበር ግጭት ሲነሳ በጋራ ባህል በመፍታት በጉዳ ሲተሳሰሩ ኖረዋል፡፡ የስልጤ ህዝብ ከኦሮሞ ያለውን ጠንካራ ትስስር ለማሳየት “አደምነት ዬለይ ስልጥነት ኤለይ ” ይላል ማለትም የአደምነት ኦሮሞነት ዘር የሌለው ስልጤነትንም የለውም እንደማለት ነው፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስልጤዎች ከዝዋይ በስተሰሜን አለምጤና አካባቢ ከሰፉው ኦሮሞ ህዝብ ጋር በማህበራዊ ህይወት ተሳስረው በሰላም እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በ16ኛው ክ/ዘመን የስልጤ ህዝብን ሲመሩ ከመጡት ታዋቂ አባቶች አንዱ ሸህ ነሰረላምህ ወደ ጅማ አካባቢ በመሄድ እስልምናን አስተምረዋል፡፡ በዚህም በጅማ ኦሮሞና በስልጤ ህዝብ መካከል አንድነት እንዲፈጠር መሠረት ሆነዋል፡፡ በ19ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ ጠንካራ የነበረው የአባ ጅፋር እስላማዊ አስተምሮ ማዕከልም በርካታ ለሆኑ የስልጤ ኡለማዎች የሀይማኖት ትምህርት በመስጠት በህዝቦቹ መካከል ጠንካራ አንድነት እንዲፈጠር አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡

በጥቅሉ በስልጤና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል ያለው ጠንካራ የባህል፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትስስር በኩሻዊው ኦሮምኛ ቋንቋና በሴማዊው ስልጢኛ ቋንቋ መካከል አሁን ለሚታዩት በርካታ የቃላት መመሳሰልና አንድነት መፈጠር ምክንያት ከመሆኑም በተጨማሪ በህዝቦቹ መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲኖር ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

የስልጤና የአማራ ህዝብ ግንኙነትና አንድነት

የስልጤና የአማራ ግንኙነት በንጉስ አምደ ፅዮን ዘመን እንደጀመረ ኘሮፌሰር ብራውካምፐር(2001፡55፡56) ይገልፃሉ፡፡ በስልጤ ትውፊታዊ መረጃም (Oral Traditions ) ንጉሥ ዘርያዕቆብ (r-1465) በስፋት ይጠቀሳሉ፡፡ንጉሱ የሀዲያ ጥንታዊ መንግስትን ለመቆጣጠር ሲያደርጉ በነበሩበት እንቅስቃሴ ወደ ስልጤ አካባቢ ይመጡ የነበረ ሲሆን አጤ ዲሰን ወይም ዲሰን ጎሳ ከአማራ ህዝብ እንደሚገናኝ በስፋት ይነገራል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የስልጤና የአማራ ህዝቦች ግንኙነት የተጠናከረው ከ19ኛው ክ/ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሸዋ አካባቢ መሪ የነበሩት ንጉስ ሳህለ ስላሴ (1814-1834) የስልጤ አካባቢን በቁጥጥር አዋሉት፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በምርኮ ተይዞ ወደ መራህቤቴ፣ አንኮበርና የተለያዩ የሸዋ አካባቢዎች ሠፈረ፡፡ በንጉስ ሳህለ ስላሴ አካባቢው በቁጥጥር ከዋለ ወዲህ ንጉሱም ከገን ስልጤ የልጅ ልጅ ከሆኑት አዝማ ቹንቡል ከሆኑት አዝማ ቀልቦ ልጅ እቴ ወሬጌ ጋር የጋብቻ ትስስር እንደፈጠሩ የዶ/ር ደርክ (2011) ጥናት ይገልፃል፡፡ በንጉስ ሳህለስላሴና በእቴወረጌ የጋብቻ ግንኙነት እነ ራስ ካሳና ራስ ዳርጌን ጨምሮ በርካታ የንጉሳን ቤተሰቦች ተወልደዋል፡፡

ከዚህና ከላይ ከተጠቀሱት ግንኙነቶች በመነጨ በርካታ የአማራ ተወላጆች ዘራቸውን ከስልጤ ይቆጥራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ቁጥር ያላቸው የስልጤና የአማራ ህዝቦች በጋብቻና በሌሎች ማበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ተሳስረው በስልጤና በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በሰላምና በፍቅር እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ ከላይ በመግቢያው እንደተለገለፀው በጣሊያን ወረራ ወቅት በስልጤ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች የስልጤ ባህላዊ አስተዳደር አካል እንዲሆኑና ከስልጤ ህዝብ በሰላምና በፍቅር ለመኖር ቃልኪዳን ተሳስረዋል፡፡

የስልጤና የሀረሪና የዛይ ህዝቦች ግንኙነትና አንድነት

የስልጤ ህዝብ በቋንቋ ፣ በታሪክ ፣ በባህልና በስነልቦና ረገድ ከሀረሪና እና የዛይ ህዝቦች ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለው ፡፡ የሀርላ ህዝብ የስልጤና የሀረሪ ህዝቦች የግንኙነት መሠረት እንደሆነ በ2ዐዐዐ ዓ/ም የታተመው “ሀረሪ- ስልጤ፡ የሀረሪና የስልጤ ህዝቦች ታሪካዊ ትስስር” በሚል በሀረሪ ህ/ብ/ክ መንግስት የባህል ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ መፅሀፍ ያትታል፡፡ የአብዱልፈታ ሁልደር (1994) መፅሀፍም የሀርላ ህዝብ ለስልጤና ሀረሪ ህዝቦች አገናኝ ድልድይ እንደነበር ይገለፃል፡፡

የስልጤ ህዝብ ከሱማሌና አፋር ህዝቦች ያለው ግንኙነትና አንድነት

በስልጤ ህዝብ ዘንድ በስፋት የሚነገረው የዘር ግንድ ቆጠራ መረጃና የሀርላን ህዝብ አስመልክቶ በስፋት የሚናገው የትውፊት መረጃ እንደሚያሳየው የሀርላ ህዝብ የስልጤ ህዝብን በመመስረት ሂደት የመጀመሪያው ማህበረሰብ ቢሆንም በዚህ የዘር ግንድ ቆጠራ መሠረት የስልጤ ህዝብ ከኦጋዴን ሶማሌዎችና የአፋር ህዝቦች ጋር በዘር እንደሚገናኝ ይጠቁማል፡፡ ጀርመናዊው ኘሮፌሰር ብራውከምፐር (2001፡28 ) የሚከተለውን ይላሉ፡-

“According to a wide spread tradition in south East Ethiopia, there were two ancestors bearing the name Djabari: Ahmed and Ismail who were commonly considered as brothers. Ahmed’s decendants are said to live mainly north of Awash and Ismail’s south of that river. The Somali of Ogaden /Darod/ and thier Oromized fracitions in the region of Hararge in particular claim thier orign from Ismail who is placed in their genologies twenty to twenty five generetions ago .The story of Djabarti ancestory is not limited to the Somali who sarted their vigorous expantion from the coastal regions toward the interior relatively late .That is hardly before the 17th century. But it is also found among the Afar and inconection with the Harla tradition …. ”ይህም ማለት በስፋት በትውፊታዊ መረጃ እንደሚነገረው ጀበርቲ በአህመድና እስማኤል ዘራቸውን ለሚመዙ ህዝቦች ቅድመ አያት ተደርገው ይቆጠራሉ ፡፡

አህመድ ጀበርቲና እስማኤል ጀበርቲ ወንድማማች ሲሆኑ አህመድ ጀበርቲ በሰሜናዊ የአዋሽ ወንዝ ዙሪያ ለሚኖሩ ህዝቦች ቅድመ አያት ናቸው፡፡ የእስማኤል ጀበርቲ ዝርያዎች ደግሞ በወንዙ ደቡባዊ ክፍል በስፋት ስፍረው ይኖራሉ፡፡ ዳሮድ በመባል የሚታወቁት የኦጋዴን ሶማሌዎች ዘራቸውን ከእስማኤል ጀበርቲ ሲመዙ ፡ በዘር ቆጠራ ሂደት ውስጥ ከሀያ እና ሀያ አምስት ትውልድ ድረስ የኦጋዴን ሶማሌዎች እስማኤል ጀበርቲን ይጠቅሳሉ፡፡ ጀበርቲን በዘር ግንድ ውስጥ የቅድመ አያትነት ታሪክ በሶማሌዎች ብቻ ተገድቦ ሳይቀር የአፋርና የሀርላ የትውፊት መረጃዎችም ጀበርቲን ይጠቅሳሉ፡፡ “

እስማኤል ጀበርቲን የሶማሌ ፣ አፋርና የሀርላ ህዝቦች የጋራ አባት እንደሆኑ ሲገልፅ የስልጤ ህዝብም እስማኤል ጀበርቲን በዘር ሃረግ ትንተና ከ7-9 ትውልድ ድረስ ይጠቅሳቸዋል፡፡ ሀጂ አልዬ -ሐጂኡመር - ሀጅ እስማኤል-ጀበርቲ---ወዘተ እያለ የዘር ሀረግን የስልጤ ህዝብ ይዘረዝራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የገራድ የአስተዳደር ሥርዓት በሶማሌና በስልጤ ህዝብ ዘንድ የባህላዊ አስተዳደር አካል ሆኖ እስካሁን መዝለቁ የግንኙነቱ አንዱ ማሳያ ሊሆን እንደሚችልም ይታመናል፡፡