የሐጂ አልዬ መስጂድ

ሐጂ አልዬ የስልጤ ብሔረሰብ ቀደምት አባት ሲሆኑ በህይወት በቆዩባቸው ዘመናት 6 ልጆችን ማለትም ገንስልጤ፣አቤቾ፣ኦየቴ ፣ ሰመረዲን፣ ዲላጳና አለቄሮ የተባሉ ልጆችን አፍርተው የነዚህ ቤተሰቦች ስብስብ የስልጤ ብሔረሰብን እንደሚፈጥሩ አንዳንድ አፈታሪኮች ያስረዳሉ፡፡

ሐጂ አሊዬ ስልጤ አካባቢ ሲደርሱ ያረፉበት ቦታ የአሁኑ የምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ታች ኡምናን አካባቢ እንደሆነ የብሔረሰቡ ታሪክ አዋቂዎች ይገልፃሉ፡፡ አመጣጣቸው ከእስልምና ሃይማኖት ጋር መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ለሳቸው መታሰቢያ የሚሆን በስማቸው የተሰየመ አንድ መስጂድ ይገኛል፡፡ የሐጂ አልዬ መስጂድ ማለት ነው፡፡

የሐጂ አልዬ መስጂድ የሚገኘው በምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ በታች ኡምናን ቀበሌ ከዞኑ ዋና ከተማ በስተምዕራብ አቅጣጫ በ50 ኪ.ሜ እንዲሁም ከወረዳው ዋና ከተማ ቂልጦ ደግሞ በ5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው፡፡ መስጂዱ በአዘርነት በርበሬ ሰንሰለታማ ተራራ ስር ከመገኘቱ በተጨማሪ ሐጂ አልዬ ለመጀመያ ጊዜ ያረፉበትም ቦታ ጭምር እንደሆነ ይነገራል፡፡ እስከ መስጂዱ የሚያደርስ በጋ ብቻ የሚያስገባ የገጠር የመኪና መንገድ አለ፡፡

የሐጂ አልዬ መስጂድ በዞኑ ከሚገኙ ማንኛውም መስጂዶች ጥንታዊ ከመሆኑም በተጨማሪ የብሔረሰቡ ቀደምት አባት የሰላት መስገጃ ( ፀሎት ማድረሻ ) ቦታ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሐጂ አልዬ መጀመሪያ ያረፉትም ሆነ መጨረሻ የሞቱት እዚሁ አካባቢ መሆኑን በቦታው ያለው የእሳቸው መካነ መቃብር ያስረዳል፡፡ መቃብሩና መስጂዱ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉ፡፡ የሐጂ አልዬ መስጂድ ዘመን እየተቆጠረ ሲሄድ በአዲስ መልክ ከመሰራቱ በቀር ከድሮ ጀምሮ እዛው ቦታ ነው የሚገኘው፡፡ የሐጂ አልዬ መስጂድ በአሁኑ ሰዓት በሁለት አይነት ሁኔታ ያለ ሲሆን በዕድሜ ረዥም የሚባለው በሳር የተሠራ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በቆርቆሮ የተሠራ ነው፡፡

በመስጂዱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሐጂ አልዬ ጊዜ የሰላት ጥሪ አድራጊ ( ሙአዚን ) የሚቆምባት እንደሆነች የሚነገርለት አንዲት ድንጋይ እስካሁንም ያለች ሲሆን ከመስጂዱ ግቢ ወደታች በመደዳ የተደረደሩት ድንጋዬች ደግሞ ከውዱዕ በኃላ መረማመጃ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በመስጂዱ ውስጥ ቀድሞ የተለያዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ተግባሮች ይከናወኑበት የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሃይማኖታዊ ተግባሮች ይፈፀምበታል፡፡ ከሐጂ አልዬ መስጂድ በቅርብ ርቀት በአልቾ ውሪሮ ወረዳ ውስጥ ደግሞ ተመሳሳይ ይዘት ያለው የሐጂ አልዬ ልጅ በሆኑት በገን ስልጤ ስም የተሰየመ ጥንታዊ መስጂድ ይገኛል፡፡

Map Location
ተመሳሳይ መስህቦች
ታግ
በማህበራዊ ሚዲያ ይቀላቀሉን
Subscribe ያድርጉ

በየ እለት የሚለቀቁ ዜናዎች ይደርስዎታል