የአሳኖ ትክል ድንጋይ/Asano Stelae ፡-የአሳኖ ትክል ድንጋይ በስልጤ ዞን በስልጢ ወረዳከ ዋና ወራቤ በሚወስደው መንገድ 8ኪ/ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ትክል ድንጋዮቹ በቁጥር ከ3 የሚበልጡ ሲሆን የዋናዉ ትክል ድንጋይ መጠነ-ዙሪያ 1ሜትርና ቁመቱ 2 ሜትር ይገመታል፡፡ የሰው ልጅ የሰውነት ክፍል የሆኑትን ዓይን፣አፍ፣እጅ፣ጡት፣ደረት፣ሆድ የማይነበቡ ፅሁፎችና የስንቅ ወይም የጦርመሳሪያ /መያዣ/ ወዘተ ... ምስሎች ተቀርጸው የሚገኙበት ነው፡፡
በሌሎቹ ላይ ደግሞ የመገልገያ መሳሪያዎች የሚመስሉ ምስሎች የተቀረጸበት ነው፡፡ሌላው ከዚሁ አካባቢ ተወስዶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በክብር በግልጽ ቦታ ተተክሎ የጥናትና ምርምር አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ትክል ድንጋይ የዚሁ ትክል ድንጋይ አካል እንደሆነ አንዳንድ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡
በጥቅሉ የአሳኖ ትክል ድንጋይ በጥንት ጊዜ በአካባቢው ላይ ይኖር የነበረውን ማህበረሰብ ስነ-ጥበብ የሚያንፀባርቅ ትክል ድንጋይ ነው ፡፡ ጎብኚዎች ብዙ ሳይቸገሩ ከቅበት ወደ ወራቤ ጉዞ ላይ አሳኖ ቀበሌ እንደደረሱ በመንገዱ ከ100ሜ ባልበለጠ ጉዞ እነኚህን ድንጋዮች ማየት የሚችሉበት አጋጣሚ በመሆኑ የሰው ዘርንየሥነ-ጥበብ ውጤቶች ቁልጭ ባለ ሁኔታ ተረድተው ይመለሳሉ፡፡