Post Thumbnail
የወራቤ ከተማን የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ተጠቆመ!

በወራቤ ከተማ አስተዳደር የሚገነባውን የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ለማስጀመር በገቢ አሰባሰብ ስራው ዙሪያ ከከተማው አጠቃላይ የመንግሥት ሰራተኞች ጋር የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የከተማዋን የዉስጥ ለዉስጥ አስፓልት መንገድ ግንባታ ለማከናወን የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል። በእቅድ ደረጃ የተያዘውን የአስፓልት መንገድ ግንባታ በአጭር ጊዜ ዉስጥ አጠናቆ ከተማዋን ከሌሎች ከተሞች ተወዳዳሪ ለማድረግ ሁሉም የበኩሉን እንዲያደርግ ተጠይቋል።

የምክክር መድረኩን የመሩት የወራቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ያሲን ከሊል በከተማዋ የውስጥ ለውስጥ አማራጭ የአስፓልት መንገድ አለመኖሩን በማንሳት ይህንንም እውን ለማድረግ የማህበረሰቡና የሌሎችም ባለድርሻ አካል ተሳትፎ ወሳኝ ነዉ ብለዋል።

ታዲያ በዚህ ትልቅ የልማት ፕሮጀክት ላይ ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ ዲያስፖራዎች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት አሻራቸዉን እንዲያኖሩ አቶ ያሲን ከሊል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ወራቤ ከተማን ለማሳደግ በርካታ የመሰዋዕትነት ትግል የተደረገ መሆኑን ያስታወሱት የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ናስር ቡሽራ አሁን ያለዉ ትዉልድ በከተማዋ ልማት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የታሪክ ተጋሪ እንዲሆን ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በከተማው እና በማህበረሰቡ ዘንድ ሰፊ የመልማት ፍላጎት መኖሩን የገለጹት አቶ ናስር ቡሽራ መዲናዋን የሚመጥን የመንገድ ልማት ስራውን እውን ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

በከተማዋ የመጀመሪያ ዙር 5.73 ኪ/ሜ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ለማሰራት ውጥን ተይዞ የዲዛይን ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን የፕሮጀክቱ ግንባታም ከ542 ሚሊየን (አምስት መቶ አርባ ሁለት ሚሊየን) ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ ተጠቁሟል።

ከተማዋን ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የተጀመረውን የልማት ስራ በማድነቅና በዚህም እጅጉን መደሰታቸውን በመግለፅ የመንገድ ግንባታ ስራውን ለመደገፍ የወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ማናቸውንም አይነት ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ሰራተኞቹ አረጋግጠዋል።

ለዚሁ ተግባር የሚውል ዛሬ በተጀመረው የገቢ አሰባሰብ ቻሌንጅ ከአመራሩ እና ከመንግስት ሰራተኛው 103,245 ብር እንዲሁም ከደሞዝ 5,886,850 ብር በድምሩ 5,990,095 ብር መሰብሰብ ተችሏል።

በከተማ አስተዳደሩ ስም የተከፈተው የገቢ ማሰባሰቢያ የንግድ ባንክ አካውንት ቁጥር 1000672357377 መሆኑን እንገልፃለን።

0 Comments

Leave A Comment